Home > Uncategorized > ‹‹መድረክ ውስጥ የኢሕአዴግን የሥልጣን ፍርፋሪ የሚፈልግ ማንም የለም››

‹‹መድረክ ውስጥ የኢሕአዴግን የሥልጣን ፍርፋሪ የሚፈልግ ማንም የለም››

‹‹መድረክ ውስጥ የኢሕአዴግን የሥልጣን ፍርፋሪ የሚፈልግ ማንም የለም››

 

አቶ ግርማ ሰይፉ፣ የመድረክ ብቸኛው የፓርላማ ተወካይ

ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በመሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የተቀላቀሉት የመድረክ አመራር አባል አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥትን አቋም ለገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መድረክንና ኢሕአዴግን የተመለከተ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡

 

ኢሕአዴግ ከመድረክ ጋር ያለ ቅድመ ሁኔታ መደራደር አለበት በሚል አቶ ግርማ ያቀረቡት ጥያቄ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር በሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ይኼንን በተመለከተና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ዮሐንስ አንበርብር አቶ ግርማን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቅርቡ መድረክን በተመለከተ አንድ ነጥብ በፓርላማ አንስተው ነበር፡፡ ለንግግራቸው መልስ ለመስጠት ሲሞክሩ ግን አልተሳካለዎትም፤ ምን ሊሉ ነበር?

አቶ ግርማ፡- ለምክር ቤቱ ጥያቄውን በጽሑፍ ስታስገባ መንግሥት አቋሙን ሊያሰማባቸው የሚፈልጋቸውን ነጥቦች ካንተ ጥያቄ ላይ ይለቅምና ቀድሞ ለአባላቱ አከፋፍሎ እንደሚያመጣ ይታወቃል፡፡ መድረክን የሚመለከት ጥያቄ በእኔ በኩል ቀርቧል፡፡ እንደተከታተልነው ግን በሌሎች አባላት የተነሳ ጥያቄን ተንተርሶ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ የተሰጠው መልስ ግን መድረክ ከኢዴፓ ጋር ቁጭ ብዬ አልወያይም በማለት ድርድሩን ረግጦ በመውጣቱ ቅድመ ሁኔታ ተጥሎበታል የሚል ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጁን ተቀብለው ካልፈረሙ የሚል መንገድ የሚዘጋ አካሄድ አስቀምጠዋል፡፡

አንደኛ እውነቱ ይኼ አይደለም፡፡ ሲጀመር የምርጫ ሥነ ምግባር ኮድ አይደለም፤ አዋጅ ነው፡፡ ግን ትክክለኛ ስሙ ደንብ ነበር፤ መጀመሪያ በደንብ ተዘጋጅቶ አዋጅ ይሁን ብለው ሲከራከሩ በነበረበት ጊዜ ነው እንሳተፋለን አንሳተፍም የሚል ውይይት የነበረው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እንዳሉት እኔ በወቅቱ ለፖለቲካው አዲስ አልነበርኩም፡፡ እንፈርማለን አንፈርምም የሚል ነው እንጂ የመጣው ከኢዴፓ ጋር ቁጭ ብለን አንወያይም የሚል ነጥብ አይደለም፡፡ አንደኛ ይህ ጉዳይ ቢኖር እንኳን ኢሕአዴግ አይመለከተውም፡፡ ከኢሕአዴግ ጋር እንነጋገር ብለን እንጂ ጥያቄውን ያቀረብነው ከኢዴፓ ጋር አይደለም፡፡ ስንፈልግ ኢዴፓ ጽሕፈት ቤት ነው መሄድ ያለብን፡፡

አሁንም የሥነ ምግባር ሕጉን ወደ ሌላ አቅጣጫ መርተውት ለሕዝብ በቴሌቪዥን ጉዳዩ ከኢዴፓ ጋር መነጋገር እንደሆነ አስመስለው ለኢዴፓ ማስታወቂያ አድርገው የሚጠቀሙበት ከሆነ ሌላ ነገር ነው፡፡ ኢዴፓ አቋም ካለው በራሱ ነው አቋሙን መግለጽ ያለበት፡፡ ኢሕአዴግ ለአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ የዚህን ያህል ጥብቅና የሚቆምበት ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ እኛ ያለ ቅድመ ሁኔታ እንደራደር ነው ያልነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ጥያቄ መልስ ጋር ተሸጉጠው የቀረቡ እንደ ሥልጣን በአቋራጭ የሚሉ ነገሮች አሉ፡፡ ምናልባት ዕድል ቢሰጠኝ ላስተላልፈው የምፈልገው መልዕክት በምንም ዓይነት አቋራጭ ሥልጣን እንደማንፈልግ፣ ምናልባትም እኛ እየነገርናቸው ያለነው ሥልጣን ወድቆ እንኳን ብናገኝ እንደማናነሳው ነው፡፡

እንዳይጥሉት ግን እንመክራቸዋለን፡፡ እንደ መንግሥት በአግባቡ ሥልጣንን የምንረካከብበት ሥርዓት ይኑር እንጂ ያልነው በአቋራጭ ሥልጣን የሚፈልግ ወይም የኢሕአዴግን የሥልጣን ፍርፋሪ የሚፈልግ መድረክ ውስጥ የለም፡፡ ሌሎች ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል፡፡ ሕገ መንግሥቱን የተከተለ አሠራር ይኑር ነው ያልነው፡፡ ካቃታቸው ማስረከብ ይችላሉ፤ ለሕዝብ ያስረክቡና አዲስ ምርጫ አድርገው መረካከብ ይቻላል፡፡ ይህም ግን በእነሱ እጅ ነው ያለው፡፡ ተዝረክርከው ቢጥሉት ግን ይህች አገር አደጋ ላይ ነው የምትወድቀው፤ ይህ ያስጨንቀናል፡፡

ሪፖርተር፡- መድረክ ከምርጫ ሥነ ምግባር ደንቡ ተሳታፊነት የወጣበትን ምክንያት አቶ ኃይለ ማርያም እንዳሉት አይደለም ብለውኛል፤ የነበረውን እውነት ያስታውሱኛል?

አቶ ግርማ፡- ኢሕአዴግ የሥነ ምግባር ኮዱን ደንብ ብሎ ይዞት ሲመጣ ደንብ የማውጣት ሥልጣን የላችሁም፡፡ ደንብ ማውጣት የሚችለው ምርጫ ቦርድ ነው የሚል አቋም ተይዞ ነበር፡፡ መድረኩን ራሱ ምርጫ ቦርድ ይምራው የሚል ክርክርና ሰነዱን የራሱ ያድርገው የሚል ክርክር ነበረው፡፡ ምክንያቱም ፓርቲዎች ደንብ የማውጣት ሥልጣን የለንም፤ ኢሕአዴግም አይችልም፡፡ ሐሳብ ማመንጨት ይችላል ነገር ግን ይህንን ሐሳብ ለምርጫ ቦርድ ነው ማቅረብ ያለበት፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ ያንን ደንብ ማውጣት አለበት ብለን ነበር ስንከራከር የነበረው፡፡ ምርጫ ቦርድ በወቅቱ አልተዘጋጀም አቅምም የለውም ነበር፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ በአቋራጭ አዋጅ አድርጐት አፀደቀው፡፡ አዋጅ ከሆነ ደግሞ አዋጁ ልክም ይሁን አይሁን ሁሉም ሰው ይገዛበታል፡፡ በዚህ ሕግ ላይ መፈራረም ለእኛ የማይረባ ነው የሆነብን፡፡ ምክንያቱም አዋጅ ሆኖ ወጥቷል፤ እንገዛበታለን፤ እንተዳደርበታለን፡፡ ነገር ግን አሁን ፈርሙ ሲባል ትርጉም አይሰጥም፡፡ እኛ የወንጀለኛ ሕግ ሲወጣ አልፈረምንበትም፤ ግን እንጠየቅበታለን፡፡ እንደዚህ ከሆነ እኮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተሰብስቦ በሕገ መንግሥቱ አምናለሁ እያለ መፈረም አለበት፡፡ ስለዚህ መፈረም ምንም ሥነ አመክኖአዊ ምክንያት የለውም፡፡ አለመፈረምም እንዲሁ ምክንያታዊ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ካልፈረማችሁ አንደራደርም ብሏል፡፡ እናንተ ደግሞ ባንፈርምበትም ሕግ ሆኖ ስለወጣ የምንገዛበት ነው፤ መፈረም የሚለው ቅድመ ሁኔታ አያስፈልግም ነው የምትሉት፡፡ ስለዚህ በዚሁ አቋም ነው የምትቀጥሉት?

አቶ ግርማ፡- እኔ አሁን የፓርቲው አቋም አመንጪ አይደለሁም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያለውን የፓርቲውን አቋም ከገለጹልኝ ብዬ ነው?

አቶ ግርማ፡- አሁን ያለውን የፓርቲዬን አቋም እኔ አይደለሁም የማስቀምጠው፡፡ የግል አስተያየቴን ከጠየቅከኝ ብንፈርምም የሚያመጣው ነገር የለም፤ አለመፈረምም ትርጉም የለውም፡፡ ትርጉም በሌለው ጉዳይ ኢሕአዴግ አጥር ለመዝጋት ብሎ የሚያደርገው ነገር ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን አይዲኤ የተባለው ድርጅት የሠራው የምርጫ ሥነ ምግባር ሰነድ ሦሰት ፓኬጆች አሉት፡፡ ኢሕአዴግ ግን ነጥሎ ያመጣው አንዱን ነው፤ ቀሪ ሁለት ፓኬጆች አሉ፤ እነሱ ይጨመሩ ነው የምንለው፡፡ ምክንያቱም በጣም ጠቃሚ ስለሆኑ ጉዳዮች ነው የሚያስረዱት፡፡ ስለ ምርጫ አስተዳደር የመሳሰሉ፤ ነገር ግን አይፈልጉም፤ ምክንያቱም ምርጫ ቦርድ ወንድማቸው ሊነካባቸው ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ጠንካራ አስተዳደር እንዲኖረው አይፈልጉም፡፡

ሪፖርተር፡- የተቃዋሚ ፓርቲ ብቸኛው የፓርላማ ተወካይ እንደሆኑ ይታወቃል፤ ፓርቲዎት እንዲያነሱት የሚፈልገው ነገር አለ፤ እርስዎ ማንሳት የሚፈልጉትም ይኖራል፤ ከዚህ ውጭ ደግሞ የፓርላማው አሠራር አለ፤ በዚህ ውስጥ ሆነው ፓርቲውን በትክክል በፓርላማው ውስጥ ወክዬዋለሁ ብለው ያስባሉ?

አቶ ግርማ፡- ጥያቄው በብቃት ተወጥተኸዋል ለማለት ከሆነ ከብዶኝ የተውኩት ነገር የለም፡፡ የምክር ቤቱ አሠራር ገደብ ያደርጋል ወይ ከሆነ አዎ፡፡ ክርክር አናደርግም፤ የሐሳብ ፍጭት የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ኅብረተሰቡ ግልጽ የሆነ ሐሳባችንን አያገኝም፡፡ ፓርላማ ማለት በትርጉም ደረጃ እኮ የክርክር ቤት ማለት ነው፡፡ አሁን ግን የጥያቄና መልስ ቤት ነው እየሆነ ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- በምክር ቤቱ በቅርቡ ያነሱት መድረክን የተመለከተ ነጥብ አለ፡፡ ኢሕአዴግ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከመድረክ ጋር ድርድር ማድረግ አለበት የሚል፡፡ ይህ ነጥብ የግልዎት ብቻ እንደማይሆን አስባለሁ፤ ፓርቲው እንዲያነሱት የሚፈልገው ነው፡፡ መድረክ ይህ ቅድመ ሁኔታ ካልተነሳ ምንድን ነው አማራጩ?

አቶ ግርማ፡- እኔ የመድረክ የፖለቲካ አቋም አመንጪ አይደለሁም፡፡

ሪፖርተር፡- ሐሳቡን ወደ ፓርላማ ይዘው ሲመጡ አጠቃላይ የፓርቲውን አቋም የተመለከተ ዕውቀት ይኖርዎታል ብዬ ነው፡፡

አቶ ግርማ፡- በሚዲያ ሊወጣ በሚያስችል ሁኔታ በጉዳዩ ላይ አልተነጋገርንም፡፡ ስለዚህ ለሚዲያ ሊደርስ የሚችል ወሬ የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- በግልዎስ ምን መሆን አለበት ይላሉ?

አቶ ግርማ፡- ቀደም ሲል እንደነገርኩህ ነው፡፡ አለመፈረማችን ትርጉም የለውም አዋጅ እስከሆነ ድረስ፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንዶች አቶ ኃይለ ማርያምን ለዘብተኛ ናቸው ይሏቸዋል፡፡ የኢሕአዴግ ፖሊሲ ባይቀየርም አብሮ መሥራት የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይቻላል የሚሉ አሉ፡፡ ይህንን ሐሳብ በፓርቲ ደረጃም ሆነ በግል እንዴት ያዩታል?

አቶ ግርማ፡- እንደ ፓርቲም፣ እንደ ምክር ቤት አባልም፣ እንደ ሰውም የማምነው ሁሉም ነገር ቋሚ ቢሆንም እንኳን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ላይ ያለው ለውጥ በራሱ ለውጥ ያመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ የለውጡ ምንጭ ምንድን ነው? የአዕምሮ ነው፡፡ አዕምሮ አልተወራረሱም ከአቶ ኃይለ ማርያም ጋር፡፡ በጽሑፍ ያስቀመጡትን ብቻ ነው የተወራረሱት፡፡ የግል የአፈጻጸምና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች በአውቶማቲክ አንድን ነገር ይቀይሩታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ግን ልዩ ለውጥ ይኖራል ብዬ አላስብም፤ ምክንያቱም የፖሊሲና የስትራቴጂ ለውጥ አያመጣም፡፡ የመፈጸሚያው መንገድ ነው እንጂ ልዩነቱ፣ ለውጡ ድራማዊ ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ አንዳንዱ ሰው በግል ባህሪው ወሳኝና በራሱ መንገድ ብቻ የሚሄድ አለ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ከሰዎች ጋር ተመካክሮ ሰውን አሳትፎ የሚሄድ አለ፡፡ እነዚህ ዓይነት ለውጦች የሚያመጡት ልዩነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ልዩ ይሆናል፡፡ በምክር ቤት ንግግሬ እንደሰማኸው የራሳቸውን አሻራ የሚያኖሩበት መልካም ዕድልን ነው የተመኘሁላቸው፡፡ ይህ መልካም ምኞት ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም እኔ በዚያ ደረጃ ላይ ብሆን የራሴ ‹‹ሌጋሲ›› እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ የአቶ ኃይለ ማርያምም በዚያ ደረጃ እንዲያድግ እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የግል አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል፡፡ በፓርቲ ደረጃስ ያለው አመለካከት ምንድን ነው?

አቶ ግርማ፡- ፓርቲያችንም እንደዚሁ ነው የሚያምነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ በዚህ ለውጥ ውስጥ በምን ዓይነት መንገድ ነው ለመንቀሳቀስ ያቀዳችሁት? የተለየ ለውጥ አለ?

አቶ ግርማ፡- ግልጽ የሆነ ነገር ነው ያለው፡፡ ንግግር እንዲኖር እንፈልጋለን፤ ለዚህ ዝግጁ ነን ብለናል፡፡ ሌላው ብዙ ሰው ግር የሚለው ነገር አለ፡፡ ከኢሕአዴግ ጋር ስንነጋገር ብዙ ሰው እንድንስማማ የሚጠብቅ ከሆነ አንስማማም፡፡ መስማማትም አይጠበቅንም፡፡ የማንስማማባቸውን ነጥቦች ሕዝብ እንዲያውቃቸው ነው የምንፈልገው እንጂ፣ ምንም ልንስማማ አንችልም፡፡ አንስማማም ስልህ ግን ነዳጅና እሳት ነን እያልኩ አይደለም፡፡ አንስማማም ነገር ግን አማራጭ ሆነን መቀጠል አለብን ነው ፍላጐታችን፡፡ እኛ ከኢሕአዴግ ጋር በፍፁም አንስማማም፡፡ የማንስማማው በምንከተለው የፖለቲካ አይዲሎጂ ምክንያት ነው፡፡ እኛ አብዮታዊ ዲሞክራሲን እስካልተቀበልን ድረስ ከእነሱ ጋር በፍፁም ልንስማማ አንችልም፡፡ እነሱ ደግሞ ወደኛ የሊበራል ዲሞክራሲ ካልመጡ ከእኛ ጋር ሊስማሙ አይችሉም፡፡ እኛ አብዮታዊ ዲሞክራሲን የመቀበል ዕቅድ የለንም፡፡ እነሱ ግን ወደ ሊበራል ዴሞክራሲ የመምጣት ዕድል አላቸው፡፡ ስለዚህ እነሱ ወደ እኛ የሚመጡበት ዕድል አለ፤ እኛ ግን ወደእነሱ የምንሄድበት ዜሮ ነው ዕድሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ያነሳሁት ጥያቄ ስለመስማማት ወይም አንዱ የሌላውን ፖለቲካ ስለመቀበል አልነበረም፡፡ ጥያቄዬ መነጋገራችሁና ለመነጋገር የምታደርጉት ጥረት እንዳለ ሆኖ እስከዛሬ አጣነው የምትሉትን የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋት ስትሉና ሊመጣ በሚችለው ለውጥ ለመጠቀም ያላችሁ ዝግጅት ምን ሊሆን ይችላል ነው?

አቶ ግርማ፡- ንግግርና ውይይት ይፈጠራል የሚል ተስፋ አለን፡፡ ይህ ጥያቄ አቶ መለስ ዜናዊ ቢኖሩም ለእሳቸው ይቀርብ ነበር፡፡ እኔ ምክር ቤት እስካለሁ ድረስ እሳቸው ለምክር ቤቱ ሪፖርት ሊያቀርቡ በመጡ ቁጥር እንወያይ እያልኩኝ መጠየቄ አይቆምም ነበር፡፡ ምንም ለውጥ ባይመጣ እንኳን የሚሰጡት ምላሽ ለታሪክ ሪከርድ እንዲደረግ እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁንም ጥያቄን በደንብ ግልጽ ላድርግ፡፡ በድርድር ጥያቄያችሁ ላይ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ አቶ ኃይለ ማርያም ከመምጣታቸው በፊት ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ በአቶ ኃይለ ማርያም ወደ ሥልጣን መምጣት የተወሰነ ለውጥ ይመጣል የሚል ተስፋ ካለ፣ ቢያንስ በእናንተ በኩል ያለውን ቅድመ ሁኔታ በማንሳት ሊገኝ የሚችለውን ዕድል ለመጠቀም ታስባላችሁ ነው?

አቶ ግርማ፡- ማሰብ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ የግሌን ነግሬሃለሁ፡፡ እንደ መድረክ ግን ሊያዝ የሚችል አቋም ሊኖር ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ፓርላማ ላይ ግን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከመድረክ ጋር ውይይት መጀመር አለበት ነበር ያሉት፡፡ ይህ ግር ስላለኝ ነው፡፡

አቶ ግርማ፡- አዎ፡፡ እነሱ ደግሞ ቅድመ ሁኔታ ስላስቀመጡ ነዋ?

ሪፖርተር፡- ይህ ቅድመ ሁኔታ ግን መፈረምን የሚጠይቅ ብቻ ነው?

አቶ ግርማ፡- በዚህ ቅድመ ሁኔታ ላይ ፓርቲው ይነጋገርበታል፡፡ ይህ ከዚህ በኋላ የሚከናወን ጉዳይ ነው፡፡ ወደፊት ሄደህ ማወቅ ፈልገህ ከሆነ ግን አሁንም ምንም ነገር የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠቧል የሚል ወቀሳ ብዙ ጊዜ ይሰማል፤ እስኪ በደንብ ግልጽ ያድርጉልኝ?

አቶ ግርማ፡- በተጨባጭ መረጃ ልንነጋገር እንችላለን፡፡ የፖለቲካ ምኅዳር ማለት ፓርቲዎች ያላቸውን ቁመና ለሕዝብ የሚያሳዩበት መድረክ ነው እንጂ፣ የፖለቲካ ምኅዳር ጠቧል ሲባል የኢትዮጵያ መሬት ጠቧል እያልን አይደለም፡፡ ለምሳሌ ዛሬ እኔ በቴሌቪዥን ቀርቤ በምክር ቤት ያልተመለሱልኝ ጥያቄዎች ስላሉ እነዚህን ለሕዝብ ላሳውቅ ዕድል ስጡኝ ብል በጭራሽ አይሰጡኝም፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር እኔ ተናግሬ ኢሕአዴግ መልስ መመለስ ቢፈልግ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በየትኛው ቻናል ላድርግልህ ነው የሚለው፡፡ ስለዚህ ሚዲያውን በእኩል ሳይሆን እስከነጭራሹ እንዳናገኘው ነው የተደረገው፡፡

አንድ ምሳሌ ልንገርህ እኛ አንድ ስብሰባ ጠርተን ቴሌቪዥኖች መጥተው ቀርፀውን ይሄዳሉ፡፡ ለመረጃ ነው የሚቀርፁት እንጂ ሊያስተላልፉልን አይደለም፡፡ ለእኛ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የደኅንነት መሥሪያ ቤት እንጂ የሚዲያ ተቋም አይደለም፡፡ የሚቀርፁን የተሳሳትን ቀን ለፍርድ ቤት መረጃ የሚሆን ነገር ለማቅረብ ነው፡፡ ሚዲያውን ተወው፤ አዳራሽ ስጡን አልን ይህንን ለማድረግ አልሆነም፡፡ ጭራሽ ገንዘባችንን ከፍለን በሆቴሎች አዳራሽ ውስጥ ለማድረግ እንኳን አልቻልንም፡፡ ከዚያ ጋዜጣ አትመን አቋማችንን ለሕዝብ ለማሳወቅ ብንሞክር ደግሞ ብርሃንና ሰላም አላትምም አለን፡፡ ከዚህ ውጭ የፖለቲካ ምኅዳሩን መጥበብ ሊያሳይ የሚችል ነገር አለ ብዬ አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች ፓርቲዎች ግን በተወሰነ ሁኔታም ቢሆንም ስብሰባ ማካሄድ ይችላሉ፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በመንግሥት ይጋበዛሉ፤ የተለያዩ ነገሮችን ማድረግ ይችላሉ፡፡ መድረክ ለምን እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ተከለከለ ብላችሁ ትጠይቃላችሁ?

አቶ ግርማ፡- በቃ መድረክ ነዋ፤ አማራጭ ያለው፣ ሊከራከራቸው የሚችል፣ በሐሳብም፣ በፖሊሲም ልዩነቱ ግልጽ የሆነ ስለሆነ ነዋ፡፡ ሌሎቹ ፓርቲዎች ዝም ብለው ናቸዋ፡፡ በነገራችን ላይ የ2002 ምርጫ ውጤት ኢሕአዴግ 99.6 በመቶ እንዲያገኝ ያደረገው መድረክ ነው፡፡ መድረክ ባይወዳደር ኖሮ በምርጫ የተወዳደሩ ብዙ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ወንበሮችን ያገኙ ነበር፡፡ ለመድረክ የታጠረው አጥር ሊያሳልፋቸው አልቻለም፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከመረጡት ሚሊዮን ሰዎች መካከል ከ380 ሺሕ በላይ መራጮች መድረክን ነው የመረጡት፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ ማንን ነው መፍራት ያለበት? ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ለ50 ዓመት የመግዛት ዕቅድ አላቸው፡፡ እኛ ብቻ ነን ይህንን የምንቃወም አትገዙንም የምንላቸው፡፡ ሌሎቹ እንደ ‹‹ግሪን ፓርቲ›› ትንንሽ ወንበር አግኝተው መኖር የሚፈልጉ አሉ፡፡ እኛ ‹‹ግሪን ፓርቲ›› መሆን አንፈልግም፤ የፖለቲካ ፓርቲ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ቅድም እንደነገሩኝ መድረክ ባይኖር ኖሮ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብዛት የምክር ቤት ወንበር ቢያገኙ ፖለቲካው ሕይወት ሊኖረው አይችልም? በዚህ ከምክር ቤቱ ሊጐለብት አይችልም ብለው ያስባሉ?

አቶ ግርማ፡- ለውጥ አይመጣም፡፡ እነዚህ እኮ ለውጥ ለማምጣት ወይም የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ እኮ አይደለም ያሉት፡፡ ምን አልባት የፓርላማ ደመወዝ ሊያገኙ ይችሉ ይሆናል፡፡ ኢሕአዴጐች መፍራት ያለባቸው መድረክን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ አማራጭና የተሻለ ፖሊሲ ስላለን ነው የሚፈራን ብለዋል፤ በትክክል ሕዝቡ ዘንድ የደረሰ ፖሊሲ አላችሁ?

አቶ ግርማ፡- አዎ፡፡ እናንተ ፖሊሲ የላችሁም ልትሉን ትችላላችሁ፤ ማወቅ ከፈለጋችሁ ግን ማንበብ ነው፡፡ በትክክል ሕዝቡ ዘንድ የምናደርስበት መንገድ ግን የለንም፡፡ ስለፖሊሲዎቻችን ለምሳሌ በሚዲያ ረገድ ያስቀመጥነውን ብታይ፣ መንግሥትን እንደዚህ ተናገርክ ተብሎ የሚዘጋ ሚዲያ አይኖርም በእኛ ፖሊሲ፡፡ በእኛና በኢሕአዴግ መካከል ያለው የኢኮኖሚ ፖሊሲም ግልጽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ ምሳሌ ላይ የተመሠረተ ጥያቄ ላንሳ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሕልፈት ተከትሎ የሐዘን ስሜት የፈነቀለው የአዲስ አበባ ነዋሪ ከተማዋን አጥለቅልቋት ስትመለከቱ ራሳችሁን የጠየቃችሁት ጥያቄ አለ? በእርግጥ ኢሕአዴግ ነው መድረክ ነው አዲስ አበባ ሕዝብ ዘንድ የደረሰው የሚል?

አቶ ግርማ፡- ለምን? የአዲስ አበባ ሕዝብ ስንት ነው? ስንት ሕዝብ ነው የወጣው? በቴሌቪዥን የወጣውን ሕዝብ አይተሃል? ይህ ብቻ ነው የአዲስ አበባ ሕዝብ? ያልወጣው ሕዝብ በጣም ብዙ ነው፡፡ በዚያ ላይ የምናምን ሊጐች የተባሉት ናቸው የወጡት፡፡ የተደራጀ ኃይል አለው ኢሕአዴግ ካልከኝ አዎ፡፡ ነገር ግን አባል የሆኑትም ልባቸው ከእኛ ጋር ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ማለት ነው? የኢሕአዴግ አባላት ልብ ከመድረክ ጋር እንዴት ሊሆን ይችላል?

አቶ ግርማ፡- እኔ እኮ ሕዝብ ውስጥ ከሕዝብ ጋር ነው የምኖረው፡፡ አይዟችሁ፣ በርቱ፣ አንድ ቀን ይሆናል የሚሉን ሚሊዮኖች ናቸው፡፡ ሁለተኛ የደጋፊ ብዛት በቀብር አይለካምና ነው፡፡ በጣም የሚያስደስተኝ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ኢሕአዴጐች 99.6 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ መርጦናል ብለው ካሉ ሁለት ዓመት አልሆነም፤ ነገር ግን ራሳቸውን ይጠራጠሩ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ቦታ የለንም ብለው ይጠራጠሩ ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት ተከትሎ የሕዝቡን መነሳሳት ሲያዩ አይ ለካ አለን ይላሉ፡፡ እስካሁን ጥርጣሬ አላቸው ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጨቋኝ የፖለቲካ ሥርዓትም ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊኖር ይችላል፡፡ በዚህ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚጠቀሙ ሰዎች ፖለቲካውን ሊቀበሉ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ይህንን ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል የሚል ሥጋት የላችሁም?

አቶ ግርማ፡- አንደኛ መነሻ አስተያየትህ የተሳሳተ ነው፡፡ ሰዎች ተጠቃሚ እየሆኑ በመጡ ቁጥር ስለፖለቲካው አያገባኝም ሊሉ አይችሉም፡፡

ሪፖርተር፡- አያገባቸውም ሳይሆን ይህንን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ያመጣው ይህ የፖለቲካ ሥርዓት ነው ብለው ሊቀበሉት አይችሉም ወይ? ይህ አያሰጋችሁም ወይ ነው ጥያቄዬ?

አቶ ግርማ፡- አዎ አይችሉም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ተጠቅመዋል ወይ ነው? ዕድገት አለና የሚታይ ነው የምትል ከሆነ እሱን አንተ ትነግረኛለህ፡፡ ከምታውቃቸው ሰዎች መካከል ስንት ሰዎች ጤፍ መሸመት እንደሚችሉ ንገረኝ? ምንም ጥርጥር የለውም ብላክ ሌብልና ብሉ ሌብል የሚጠጡ ሰዎች ቁጥራቸው ድሮ ከነበረው ጨምሯል፡፡ እነዚህ ግን በሙሉ ቢደመሩ 20 ሺሕ ወይም 30 ሺሕ አይሞሉም፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ አብዛኛው የአዲስ አበባ ሕዝብ ግን ጤፍ መሸመት አይችልም፡፡ አንድ ጥናት ሥራ ለራስህ፡፡ ለጠቅላላ ዕውቀትህ፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑ ጓደኞችህን ወይም ሌሎች አጠገብህ ያሉትን የጤፍ ዋጋ ስንት ነው ብለህ ጠይቃቸው? በሬዲዮ የሰሙትን ሳይሆን በስንት ገዛችሁ ብለህ ጠይቃቸው፡፡፡ አልሸመቱም፣ አያውቁውም፡፡ ምክንያቱም መግዛት ትተዋል፡፡ ብዙው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀለብ ለመሸመት ገበያ መሄድ ትቷል፡፡ አሁን አብዛኛው ሕዝብ በየቀኑ ተሯሩጦ ያገኘውን ይዞ እንጀራ ግዥ ገብቷል፡፡ አሁን አንድ እንጀራ እስከ አምስት ብር ደርሷል፡፡ ደመወዝ ግን የዚህን ያህል አልጨመረም፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት ማለት በሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ ካላመጣ ዕድገት ነው ልልህ አልችልም፡፡

ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ለውጥ እየካድኩ አይደለም፡፡ ሕንፃዎች የሉም አልልህም፣ ሀብታም የሆኑ ሰዎች የሉም አላልኩህም፡፡ ተጠቃሚ ያልሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር እየበዛ ነው፤ እያልኩ ያለሁት ዕድገታችን ሚዛናዊ አይደለም ነው፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ከሥርዓቱ ጋር ተጣብቀው እያደጉ ነው፡፡ ሥርዓቱ ሲንገጫገጭ ግን ፍርኃታቸው ይመነጫል፡፡ አብዛኛው ኅብረተሰብ ግን ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ በ21 ዓመታት ውስጥ በምግብ ራሳችንን እንድንችል አላደረገንም፡፡ ስንዴ አሁንም እንገዛለን፡፡ ከ80 በመቶ በላይ ገበሬ በሆነበት አገር ስንዴ የምትገዛ ከሆነና ዕድገት አለ የምትለኝ ከሆነ አልስማማም፡፡ አሜሪካ ሁለት በመቶ የሆነው ገበሬ፣ 98 በመቶ የሆነውን ሕዝብ ቀልቦ ተርፎት ይሸጣል፡፡ የእኛ 80 በመቶ አርሶ አደሮች 20 በመቶ አይቀልቡም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጠቃሚ ሆኖ ኢሕአዴግን ከመረጠ ግን ችግር የለብኝም፡፡ አይሆንም ከሁሉም ኢሕአዴግ ይሻለኛል ብሎ ከመረጠ ግን ከመራጩ ጋር ጠብ የለኝም፡፡ አሁን አልተመቸኝም ብሎ መራጩ ድምፁን ሲያሰማ ግን አማራጭ ሆነን መገኘት ነው የእኛ ሥራ፡፡

ሪፖርተር፡- የበለጠ እናብራራው፡፡ አሁን ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ደርሷል ሳይሆን፣ በዚሁ ከቀጠለ ሊደርስ ይችላል፡፡ በዚህ ሒደትና ጊዜ ውስጥ እናንተ የተሻለ አማራጭ መሆናችሁን ካላሳያችሁ የኢኮኖሚ ጥቅሙ ሙሉ ለሙሉ ወደ ኅብረተሰቡ ደርሶ እንድትዘነጉ አያደርጋችሁም?

አቶ ግርማ፡- እኛ ምንም አንሰጋም፡፡ አሁን እከሌ ተጠቅሟል በሚቀጥለው ደግሞ እኔ እጠቀማለሁ ብሎ ወረፋ የሚይዝ ከሆነ ይሁን ጥሩ ነው፡፡ እኔ ግን እያልኩ ያለሁት ለአምስት ዓመት ይህን አገር ለማስተዳደር ዕድል ቢሰጠን ቢያንስ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምግብ ራሱን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- እሺ ይህንን ተንተን አድርገን ለአንባቢዎቻችን  እናስረዳ፡፡ በአሁኑ ወቅት የፓርላማ አባል ነዎት፡፡ አብዛኛውን ጊዜዎትን በግል ሥራዎ ላይ በማጥፋት ገቢ ያገኛሉ፡፡  መድረክ ሥልጣን ላይ ነው ብለን ብናስብ የእርሶ ገቢ አሁን ካለው በምን ያህል ሊበልጥ ይችላል? የመድረክ መምጣት በእርሶ ሕይወት ውስጥ ሊፈጥር የሚችለውን እስኪ ይንገሩኝ?

አቶ ግርማ፡- እኔ ለግሌ ጥቅም ስል አይደለም የምሠራው፡፡ በግሌ ምንም ችግር የለብኝም፡፡ መድረክ ሥልጣን ሲይዝ አንድ ሳንቲም ላይጨምር ይችላል፡፡ የምንከተለው ፖሊሲ ግን በጣም ብዙ ሥራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ ባለሀብቶች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ሚሊዮኖች የሥራ ዕድሎችን እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ እነዚህ የሥራ ዕድሎች ሕዝቡ ምግብ እንዲበላ ያደርጉታል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከኢሕአዴግ በዋነኝነት የምንለየው ግን በዚህ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ስኳር ፋብሪካ ራሱ ገንብቶ ራሱ ነው የውጭ ምንዛሪ የሚወስደው፡፡ ስኳር ፋብሪካውን እኔና አንተ ብንይዘው ግን የውጭ ምንዛሪው ለአገር ነው የሚሆነው፡፡ ኢሕአዴግ ከዜጐቹ ጋር ውደድር የገባ መንግሥት ነው፡፡ እኛ ይህንን አናደርግም ገንዘብ ቢኖረን ለባለሀብቱ እንሰጥና ባለሀብቱ ይሠራዋል፡፡ ይህ በከተማ ደረጃ ያለንን ነው የምነግርህ፡፡ በግብርና ደረጃ ስመጣ ደግሞ በመጠባበቅ የሚታረሱ መሬቶች ሁሉ ይታረሳሉ፡፡ ዜጐቻችን ምግብ ገዝተው ይበላሉ፡፡ ይህንን በአምስት ዓመት እናደርጋለን ነው የእኛ ዕቅድ፡፡ ይህንን ካላደረግን በቃ ከሥልጣን መውረድ ነው፡፡ ስንዴማ አንገዛም፡፡ ስንዴ አለመግዛትማ የክብራችን ጉዳይ ነው፡፡ የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ስንዴ መግዛት ስለሚችል አይመስልዎትም? ሌሎች እንደ ሳውዲ ዓረቢያ ያሉ አገሮች እኮ ይገዛሉ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በግብርና የተሰማሩ ሌሎች አገሮችም ወደ ራሳቸውም ይልካሉ፡፡

አቶ ግርማ፡- የውኃ ማማ በምትባል አገር ውስጥ ስንዴ መግዛት ኢኮኖሚው ስላደገ ነው ሊባል አይችልም፡፡ በቂ ክምችት መያዝ አለብን፣ በቂ ምርት ማምረት አለብን፡፡ ሦስት ወር ዝናብ ካልዘነበ እኮ ድርቅ ምናምን ነው የሚባለው፡፡ ከዚህ አዙሪት መውጣት አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን እያሉኝ ያሉት የኢትዮጵያ ሕዝብ በችግር ውስጥ ነው፡፡ ነፃነት የለውም፤ የሚበላውም የለውም፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓመት በአዲስ አበባ በሚካሄደው ምርጫ መድረክ የበለጠ ድምፅ ያገኛል? አዲስ አበባን የማስተዳደር ሥልጣን ሊይዝ ይችላል?

አቶ ግርማ፡- ምርጫው ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ከሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ አይ ተጠቅሜያለሁ ብሎ ካልመረጠን ቅር አይለንም፡፡ ግን ምንም ጥርጥር የለንም፡፡ ሕዝቡ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለመድረክ ድምፁን እንደሚሰጥ አልጠራጠርም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሌላ ፖለቲካዊ ጉዳይ እንሂድ፡፡ አቶ ኃይለማርያም በተደጋጋሚ የሚያነሱት ሁለት ባርኔጣ የማድረግን ጉዳይ፡፡ ይህ ጉዳይ በአቶ መለስ ጊዜም የነበረ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በተለይ እናንተን የሚመለከተው ለምንድን ነው?

አቶ ግርማ፡- እነዚህና እነዚህን የመሰሉ ጉዳዮች ናቸው ትንሽ ተቀራርበን እንሥራ እንድንል ያደረጉን፡፡ ሁለት ባርኔጣ እንደሌለን ማወቅ አለባቸው፡፡ ተቀራርበን ስለማናውቅ ይገምታሉ፡፡ በመሆኑም ይሳሳታሉ፡፡ ደኅንነቶቻቸው ትክክለኛ መረጃ አይሰጧቸውም ማለት ነው እንጂ ሁለት ባርኔጣ የሚባል ነገር አናውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ እውነት አለ መንግሥት የመረጃና የደኅንነት መሣሪያዎቹ በእጁ ናቸው፡፡ እነዚህ እያሉ ከመንግሥት እይታ ውጭ መሆን ይከብዳል፡፡ ሌላው ደግሞ የእናንተኑ አባል ፍርድ ቤት አቅርቤ አስፈርጄበታለሁ እያለ እኮ ነው?

አቶ ግርማ፡- አንዱዓለም አራጌ የፓርቲያችን አባል ሁለት ባርኔጣ አድርጓል፡፡ ፓርቲው ውስጥ ተጠልሎ ሌላ ሥራ እየሠራ ነበር የሚል ተጨባጭ መረጃ ለእኔ ቢሰጡኝ የመጀመሪያው ጠላቴ አንዱዓለም ነው፡፡ አንዱዓለም ላይ አንዲት መረጃ የላቸውም፡፡ ሁለት ባርኔጣ አድርጓል ሲሉ እነሱን ውሸታም ከማለት ውጪ ምን ታደርጋቸዋለህ? አንድም ማስረጃ አላገኙም፤ ፍርድ ቤት ቆሜ ልነግርህ እችላለሁ፡፡

ይህ የሚያሳስር ከሆነ እኔን ይክሰሱኝና ይሰሩኝ፡፡ እኛ ፓርቲ ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ከሌላ ቡድን ጋር ግንኙነት ሊመሠርቱ አይችሉም ብለን ልንፈርም አንችልም፡፡ ሰዎች ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ በሰላማዊ መንገድ ትግል የሚያደርጉ ሰዎችን አያበረታታም፡፡ ስለዚህ ሰዎች ሰላማዊ ወዳልሆነ አማራጭ ይሄዳሉ፡፡ ባርነት በቃኝ ብለው ይሄዳሉ፡፡ ልክ እነሱ እንዳደረጉት፡፡ እነሱ ጫካ ሲገቡ ልክ ከነበሩ፣ አሁንም መንገድ የዘጉባቸው ሰዎች ጫካ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ እያልን ያለነው ይህንን መንገድ ዝጉትና የሰላማዊውን መንገድ አስፉት ነው፡፡ ሰላማዊው መንገድ ከተከፈተ ያኛው መንገድ በራሱ ይሞታል፡፡ ሰዎች ለምን አስመራ ይሄዳሉ? ሰዎች ሐሳባቸውን እዚህ መግለጽ ስላልቻሉ አይደለም? እንደ አቋም ሁለት ባርኔጣ ማድረግ አይቻልም፡፡ በሕግም አይቻልም፡፡ በፓርቲው ደንብም ክልክል ነው፡፡ እንኳን በሌላ መንገድ ከሚታገሉት ጋር በሰላማዊ ትግል ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ውስጥ አባል መሆን አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- መድረክ አባሎቹ መንግሥት አሸባሪ ከሚላቸው ከተለያዩ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ማድረግ አለማድረጋቸውን እንዴት ነው ሊያጣራ የሚችለው? መድረክን ሊያፈርሱ የሚፈልጉ ሰዎች ቢኖሩ እንኳ ይህንን አጋጣሚ እንዳይጠቀሙ እንዴት ነው የምታጣሩት?

አቶ ግርማ፡- አናጣራም፡፡ ሥራችን አይደለም፡፡ እኛ የደኅንነት መሥሪያ ቤት የለንም፡፡ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ያለው መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት እነዚህን ሰዎች እንደዚህ ሲያደርጉ ካገኛቸው ለእኛ ይንገረን የዚያን ጊዜ ዕርምጃ እንወስዳለን፡፡ አሁን ግን የያዛቸውን እነ አንዱዓለምንና ናትናኤልን በተመለከተ አንቀበልም፡፡ የእኛ አባላት ናቸው፤ ነገር ግን ትክክለኛ መረጃ አልሰጠንም፡፡ ስለዚህ የእኛ ጀግኖቻችን ናቸው፤ የነፃነት አርበኞቻችን ናቸው ብለን እናከብራቸዋለን፡፡ መንግሥት መረጃ ሰጥቶን ዕርምጃ ባንወስድ ግን ተባባሪዎች ነን ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግን ጉዳቱ አይታይዎትም? ወደ ፖለቲካው መግባት የሚፈልጉ ወጣቶች ይህንን እየሰሙ መድረክን እንዴት ይቀላቀላሉ?

አቶ ግርማ፡- ምንም ጉዳት የለውም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች ጀግና ናቸው ብለው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ጐበዞች ብለው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እኛ እሱን አይደለም የምንፈልገው፡፡ ኢሕአዴግ ሰዎች ወደኛ እንዳይመጡ ነው ይህንን የሚያደርገው፡፡

Advertisements
Categories: Uncategorized
  1. No comments yet.
  1. No trackbacks yet.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: