Home > Uncategorized > የመለስ “ተወዳጅነት” ለኢህአዴግ ምኑ ነው!? (Abe Tokichaw)

የመለስ “ተወዳጅነት” ለኢህአዴግ ምኑ ነው!? (Abe Tokichaw)

የመለስ “ተወዳጅነት” ለኢህአዴግ ምኑ ነው!?

የርዕሷ ዜማ በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ “የአክሱም ሀውልት ለደቡብ ምኑ ነው!?” ሲሉ የተናገሯትን ትመስላለች። እናም ለዜማ ኩረጃዬ ይቅርታ ጠይቄ እቀጥላለሁ።

አሁን አሁን ኢህአዴግ ምን እየሰራ እንደሆነ እጅግ በጣም ግራ እየገባኝ መጥቷል… “ገና አሁን!” ብለው ሲጠይቁኝ ይታየኛል። እኔም አይ ገና አሁን ሳይሆን አሁንም ድጋሚ በጣም ግራ እየገባኝ ነው!? እልዎታለሁ። የምሬን እኮ ነው…

አቶ መለስ ሞቱ በተባለ ሃያ አራት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አስከሬናቸው አዲሳባ ይገባል ተባለ። በነገራችን ላይ ይሄ ፍጥነት አቶ መለስ የሞቱት ቀድመው ነው። የሚሉትን ወገኖች ንግግር ይበልጥ ያጠናክረዋል። ይሄንን እንተወው እዚህ ግባ የሚባል ወሬ አይደለም። ኢቲቪም ሆነ አቶ በረከት እንደሆኑ “ሰው ያምነናል” ብለው ይናገሩ እንጂ ሁሉም በየጓዳው “አዬ..ዬ…” እንደሚለቸው እናውቃለን…!

(እንኳን ይቺንና የአበል ለቅሶ እንለያለን…!)

የሆነው ሆኖ ለአቶ መለስ በርካታ ሰው አለቀሰላቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ ትክክለኛው የአቶ መለስ አዛኞች የመጀመሪያው ቀን እየዬ ብለው ቦሌ አየር መንገድ የታዩት ናቸው። ከዛ በኋላ ይሄንን ያኽል ሰው ይመጣል ብለው ያልጠበቁት እነ ጋሽ ኢህአዴግ ልክ ባለፈው ጊዜ አቶ መለስ የዘጠና ሰባቱን የኢህአዴግ ሰልፍ ሲያዩ አቅላቸውን ስተው “ይሄንን የህዝብ ማዕበል ይዘን ማጭበርበር ሳያስፈልገን ምርጫውን እናሸንፋለን…!” እንዳሉት አይነት “ይሄንን የህዝብ ማዕበል ይዘን በለቅሶ እድገት እመርታ እናሳያለን” ብለው ለራሳቸው ቃል ገቡ። ገቡናም ለሚቀጥሉት አስራ ምናምን ቀናት ህዝቡን ለማስለቀስ ተማማሉ፤

ከዛስ…

ከዚያ ሲያስቡት ያንን ሁሉ ቀን ሰው ከየት ይመጣል? እርግጥ ነው ቤተ መንግስቱ በጎብኚዎች መጨናነቁ አልቀረም ምክንያቱ ደግሞ ቤተመንግስቱን በደህናው ጊዜ ማንም አይቶት ስለማያውቅ በዚህ አጋጣሚ መጎብኘቱ ለብዙዎች ደስታን ስለሚፈጥርላቸው ነው።

በነገራችን ላይ አንድ ወዳጃችን የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስከሬን የጫነው መኪና በህዝብ ታጅቦ ሲያይ ምን እንዳለን ነግሬዎታለሁ እንዴ…? ምን አለ መሰልዎ? “አቶ መለስ ዛሬ ገና ህዝቡን ሳይፈሩ አየኋቸው” ብሎናል… እኛም መሞት ደጉ ብለን አደንቀናል!

እዝችው ጋ ያቺን ቀልድ እናምጣት፤ አቶ መለስ ሆዬ በአንዱ ቀን ከአየር ማረፊያ መንገድ አዘግተው እየከነፉ ወደ ቤተመንግስታቸው ሲሄዱ አንዲት ሴትዬ ጭር ባለው መንገድ ላይ ድንገት ተከሰቱ፤ ይሄኔ ፌደራል ፖሊሱ ሴትዮዋን ጋማቸውን ይዞ ወደ ግድግዳ ፊታቸውን አዙሮ ክላሹን ደገነባቸው። ወይዘሮዋ ደነገጡ ሊረሽኑኝ ነው እንዴ…? ብለው በቀስታ ዘወር ሲሉ ፖሊስ ሆዬ፤ “ዙሪ ወደዛ…” ብሎ ፊታቸውን ከግድግዳው ጋር አጣበቀው…!” ልክ አቶ መለስ ካለፉ በኋላ “ከውካዋ አሮጊት… በይ ሂጂ ከዚህ…!” ብሎ ተቆጣቸው። ይሄኔ ሴትየዋ ሃይላቸውን አሰባሰበው “የኔ ጌታ ይቅርታ አድርግልኝና ሰውየውን የምትጠብቋቸው ከቡዳ ነው ከጥይት!?” ብለው ጠየቁ።

አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት እያሉ፤ “የልማት አርበኞችን” ሊሸልሙ ካልሆነ በስተቀር ከህዝብ ጋ ተቀላቅለው አይተናቸው አናውቅም። ቤተ መንግስታቸውም ቢሆን ግድግዳውን እንኳ ተጠግቶ መሄድ አይቻልም። ፎቶግራፍ ማንሳትም አይቻልም። አረ ትክ ብሎ ማየት መቻሉንም እንጃ…

ታድያ ልክ አሁን ሲሞቱ እኔ ከሞትኩ እንዳለችው እንስሳ… (ለሞተ ሰው አህያ አይባልም ብዬ ነው!) እርሳቸው ከሞቱማ ተብሎ ያለ ፍተሻ ሁሉ ቤተ መንግስት መገባቱን አይተናል። እስከዛሬ ሲጠበቁ የነበሩት ለካ እርሳቸው እንጂ ቤተ መንግስቱ አልነበረምና…!?

እኔና ሌሎች በርካቶችን የገረመን ነገር አቶ መለስ በህይወት ዘመናቸው ዱቤ እንዳለበት ሰው ሲደባበቁን ኖረው ዛሬ ከሞቱ በኋላ ተሰናበቷቸው እየተባልን አበሳችንን ያየንበት ምክንያት ነው።

ያው ባለፈው ሰሞን ለማሳየት እንደሞከርኩት በርካታ መስሪያ ቤቶች እና ቀበሌዎች ህዝቡን በደብዳቤ አንዴ “እናሳስባለን” አንዴ “እናስጠነቅቃለን” እያሉ ሲያስለቅሱት ሰንብተዋል። ግን እኮ በፈቃዱ ያለ ቀስቃሽ ያለቀሰው ሰው በቂ ነበር። ኢህአዴግ ግን ሰው አይጠግብም። ብለን ካወደስነው በኋላ በተለይ ለማስለቀስ ሲሆን በርከት ሲል ደስታው ነው ብለን ሀቁን እንናገረለን!

ለማንኛውም አሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ግባተመሬት ተፈፅሟል። አንዴ ዘቅዝቀው ሲይዙት አንድ ጊዜ ደግሞ “ጨርቅ ነው” እያሉ ሲያጣጥሉት የነበረው ባንዲራም አብሯቸው ተቀብሯል። ይሄ ታሪካዊ ስህተት ይመስለኛል። እንዲያ ያንጓጠጡት አንሶ ደግሞ አብሯቸው መቀበሩ በእውነቱ ተገቢ አይመስለኝም። (አረ እንደውም የምን አይመስለኝም ነው…!? ነውር ነው እንጂ!)

በነገራችን ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን ወደፊት ደግሞ በስማቸው በሚገነባው ወመዘክር ውስጥ እንደሚቀመጥ ተነግሮናል። ስለዚህ አቶ መለስ “ግባተመሬት” እንደተባሉት ሁሉ ገና ደግሞ “ውጣተመሬት” አለባቸው ማለት ነው…! ወይ አበሳቸው! ግን የዚህስ ጠቀሜታ ምንድነው? እሺ ወመዘክሩ ይገንባላቸው። አስከሬናቸውን ግን በዛ ቦታ እናስቀምጣለን ብሎ ማለት ባለስልጣኖቻችን በስሜት እንጂ በስሌት እየመሩን እንዳልሆነ የሚያሳይ ይመስላል…!

ለማንኛውም አሁንም ከአስራ አምስቱ ቀናት “ብሔራዊ ሀዘን” በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚያወድሱ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች አልተቋጩም። አሁንም አቶ መለስ ዜናዊ ተወዳጅ እና “ተመላኪ”  እንደነበሩ እየተነገረን ነው። መቼም አሁን ሞተዋልና እሺ ይሁንላቸው ተወዳጅ ነበሩ እንበል…! ግን ምን ይጠበስ…?

አሁንም አስከሬናቸው ይግዛን? ወይስ ምን እናድርግ…? ግራ ነው የሚያጋባው! አረ “ያልሞታችሁት” የኢህአዴግ ባለስልጣናት ቢያንስ ይቺን ቀሪ ሶስት አመት መንግስት መንግስት ምሰሉን…!

በደህናው መንገድ ምሩን እና “ተወዳጅ” ለመሆን እስቲ ዕድላችሁን ተጠቀሙ…! እንጂ በድሮው በሬ አትረሱ… በሬውም ይረፍበት!

Advertisements
Categories: Uncategorized
  1. No comments yet.
  1. No trackbacks yet.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: