Home > Uncategorized > የኤርትራ መንግስትና ኤርትራውያን ስለምን የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ህመም አስጨነቃቸው? (ነሐሴ 15 ቀን 2004 ለንባብ ከበቃው ፍኖተ-ነፃነት ጋዜጣ የተወሰደ)

የኤርትራ መንግስትና ኤርትራውያን ስለምን የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ህመም አስጨነቃቸው? (ነሐሴ 15 ቀን 2004 ለንባብ ከበቃው ፍኖተ-ነፃነት ጋዜጣ የተወሰደ)

የኤርትራ መንግስትና ኤርትራውያን ስለምን
የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ህመም አስጨነቃቸው?

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ህመም ተከትሎ በመንግስት ባለስልጣናት አንዴ “ከአስር ቀናት በኋላ” ሌላ ጊዜ ደግሞ
“በቅርብ ግዜ ስራቸውን ይጀምራሉ፡፡” እየተባልን ስንት አስርት ቀናት አሳልፈናል። እኔ በግሌ የአቶ መለስን
መንግስትና አስተዳደራቸው በጣም ከሚጠሉ ዜጎች አንዱ ብሆንም፣ ለሰውየው ግን ሞት አልመኝላቸውም።
ምክንያቱም ህመምና ሞት ለማንም ሰው የማይቀር ዕዳ ነውና። ለጤናቸው ምህረት ኩፉኛ ለታመመው
አስተዳደራቸውና ስልጣናቸው ደግሞ ሞት እመኛለሁ፣ ይሄ ምኞት በኢህአዴግ አፈና ስር ያለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ
ፍላጎት ይመስለኛል።
ለነገሩ አቶ መለስን ለዚህ ያበቋቸው ነፃነታቸውንና ህሊናቸውን ሸጠው እየኖሩ ያሉት ካድሬዎቻቸው ናቸው።
ለምን ብትሉኝ ካድሬዎቹ በየመስራቤቱ፣ በየመሽታቤቱ፣ በየአደባባዩ፣ በየቀበሌውና በየሚድያው “ኢትዮጵያ ያለ
ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እንደ ጎረቤታችን ሶማልያ ትበታተናለች፤ የማይተኩ መሪ ናቸው” ወዘተ እያሉ ውዥንብር ሲፈጥሩ መጥተዋልና ነው።
ጊዜና አጋጣሚው ደግሞ የካድሬዎቹን ውሸትና ውዥምብር ከንቱነት አጉልቶ ያሳየ ይመሰለኛል። ይሄው አቶ መለስ የሉም እኛና
ኢትዮጵያችን ግን መኖር ቀጥለናል። ኢትዮጵያ የአንድ አምባገነን መሪ ህልውና ላይ እዳልተንጠለጠለች ለካድሬዎቹ በዚህ ሁለት ወር
ያስመስከረች ይመስለኛል።
በሌላ በኩል ጠ/ሚ መለስም ሆኑ በዙሪያቸው የተሰለፉ ሰዎች ሰውየው የታመሙት በፈጠራ ክስ ተከስሰው በዕድሜ ልክ እና እስከ 18
አመት የሚደርስ እስራት የተፈረደባቸው እነ አንዱኣለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና መሰል ኢትዮጵያውያን
የሰላም ታጋዮችና ጋዜጠኞች በየእስር ቤቱ እየተጋፈጡ ያለውን ስቃይና መከራ እንዲያስተውሉ ይሆን? በማለት ራሴን እጠይቃለሁ ።
ወደ ዋና የፅሑፌ ርእስ ልመልሳችሁ፣ የአቶ መለስ መታመም ከተነገረ ማግስት ጀምሬ የነ ኢሳያስ ኣፈወርቂ ሚድያዎች ስለዚህ ጉዳይ ምን
ያሉ ይሆን እያልኩ ስከታተል እስከ አሁን ድረስ ምንም ትንፋሽ አላሉም። ታስታውሱ ከሆነ የግብፅና የሊብያ አምባገነኖች በህዝባዊ ማዕበል
ሲናወጡና ሲሽቀነጠሩ እነ ኢሳያስ ኣፈወርቂ ደስተኞች ስላልነበሩ ሚድያዎቻቸው ትንፍሽ አላሉም ነበር፡፡
ኋላ የጠ/ሚ መለስ ዜናዊን የትናንት ታሪክ ሳገላብጥ እንዲሁም በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያን በኢንተርኔትና
በVOA (አሜሪካ ራድዮ ትግርኛ ፕሮግራም) የጠ/ሚ መለስ መታመም ከልብ እንዳሳዘናቸው ሲገልፁ በሰማሁ ቁጥር የኤርትራ መሪዎችና
ሚድያዎቻቸው በጠ/ሚ መለስ መታመም ዙሪያ ለምን ዝምታ እንደመረጡ ገባኝ፡፡ እንዲያውም ብዙ ኤርትራውያን በአሜሪካ ሬድዮ
በግልፅ “ያለ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ኤርትራውያን ምን ሊከተለን እንደሚችል እናውቃለን ስለዚህ እግዚአብሔር ምህረት እንዲሰጣቸው
እንፀልይላቸው” ሲሉ አንዳንድ ጠ/ሚ መለስ ለኤርትራውያን ያደረጉትን “ውለታ” ያላወቁ ደግሞ ሀሳቡን ሲቃወሙት ይደመጣሉ።
ለመቃወማቸው ምክንያት ደግሞ “በዓለም አቀፍ ሕግ ለኛ የተፈረደብን መሬታችን (ባድመን መለታቸው ነው) በሀይል ይዞ አላሰረክብም
እያለና የዓይናችሁ ቀለም አላማረንም ብሎ ከኢትዮጵያ አንድንወጣ ያደረገ ጠላታችን ነው” ይላሉ።
ለነገሩ ኤርትራውያን ጠ/ሚ መለስን ያላከበሩና ያላመሰገኑ ማንን ያከብራሉ? ለማንስ ያመሰግናሉ? እንዲያውም እውነት እንናገር ከተባለ
ከኛ ከኢትዮጵያውያን በላይ ኤርትራውያን ሊያከብሩዋቸውና ሊያመሰግኗቸው ይገባል። ለምን የምትሉኝ ካላችሁ የሚከተሉት ነጥቦች
በደምብ እዩልኝ።
1ኛ. ነፃነት ወይም ባርነት የሚሉ ሁለት ሰማይና ምድር የሆኑ አማራጮች በማቅረብ “ሪፈረንደም” ተብየውን በማካሄድ ኤርትራ
ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል የማራቶን ሩጫ በጥዋቱ ከበረሀ ደደቢት እስከ ሚኒሊክ ቤተመንግስት በመሮጣቸው፤
2ኛ. በትረ-ስልጣናቸውን ለመጨበጥ ቋምጠው የኢትዮጵያ ህዝብ የወደ ፊት ዕጣ ሳያገናዝቡና አለማቀፍ ሕግን ወደ ጎን ትተው ኢትዮጵያ
ወደብ አጥታ ሁለት ወደቦች ባሏት ኤርትራ ላይ ጥገኛ እንድትሆን ማድረጋቸው፤
3ኛ. ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተገነጠለች በኋላም ሻአብያዎች “ኤርትራ የብቻችን ኢትዮጵያ የጋራችን” እያሉ የኢትዮጵያን ሀብት
በመቆጣጠር የበላይነታቸውን እንዲያሳዩ በሩ እንዲከፈትላቸው በማድረጋቸው። ለምሳሌ በአንድ ወቅት አንድ ዛፍ ቡና የሌላት ኤርትራ
ያለ ህግና ቀረጥ የኢትዮጵያን ቡና እንደፈለገች በመዝረፍ ቡና ወደ ዓለም ገበያ በማቅረብ ከነ ብራዚል ተወዳድራ ከዓለም 3ኛ ወጥታ
ነበር። ህገ ወጥ አካሄዳቸውን ሲቃወሙ የነበሩ ኢትዮጵያውን በኤርትራ ደህንነቶች ከአዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ መቀሌ፣ ዓዲግራት ወዘተ
ተይዘው ኣስመራ ተወስደው ሲታሰሩና ሲገደሉ የሚከራከርላቸው ወገን አልነበረም። ለምሳሌ ኢትዮጵያን መውረር ሲያስቡ መጀመርያ
ጀግናውን ሓየሎም ኣርኣያን መግደል ስለነበረባቸው ገደሉት።
ክብሮም ከመቐለ4ኛ. የኤርትራን እቅድና አካሄድ የተረዱት እነ አቶ ገብሩ ኣስራትና(በወቅቱ የትግራይ ክልል መስተዳድር ነበሩ) አቶ ስየ ኣብርሃ (የቀድሞ
መከላከያ ሚኒስተር ነበሩ) “የኤርትራ መሪዎች ሊወሩን እያሰቡ ነው፤ ከወዲሁ ጥንቃቄ እናደርግ፣ የሰራዊታችንን አቅም መገንባ አለብን”
ብለው ስጋታቸው ስለገለፁ ብቻ ጠ/ሚ መለስ ይህንን ሀሳብ “የኤርትራ መሪዎች እብዶች አይደሉም። ይሄ የጦርነት ናፋቂዎች ሃሳብ ነው”
ብለው በማብጠልጠል ለኤርትራ መሪዎች ጥሩ ዕድል በመፍጠራቸው፤
5ኛ. ከወረራ በኋላ “ሀገሬ ለምን ተደፈረች ብሎ የተቆጣ የኢትዮጵያ ወጣት ከደቡብ እስከ ሰሜን፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በአንድ ልብ
ተንተግትጎ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ እጅግ ዘግናኝ የሆነ መስዋትነት በመክፈል የተወረረውን ሉአላዊ መሬቱን ካስመለሰ በኋላ ጠላቱን
ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የያዘው የድል ጉዞ ለጠ/ሚ መለስ የማያስደስት ስለሆነ ቤተመንግስት ሆነው “ተመለሱ” የሚል
ቀጭን ትእዛዝ በማውረድ ችግሩ ሳይቋጭ እስከ አሁን የሰው ህይወትና ንብረት እንድናጣ አድርገዋል፤
6ኛ. የተደፈረ መሬታችንን በጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን አስመልሰን ስናበቃ ይግባኝ የሌለው ፍርድ እንድንቀበል በመፈረማቸውና
የሀገራችን የታሪክ ሊቃውንት(ሙሁራን) በማግለል “ሁሉን አዋቂ ነኝ” በማለት በዓለም ፍርድ ቤት የሀፍረት ካባ እንድንለብስና በመቶ
ሺዎች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መስዋእትነት ተከፍሎ የተመለሰ መሬታችንን(ባድመን) በፍቃደቸው ለኤርትራ እንዲወሰን
በማድረጋቸው፤
7ኛ. በሁለቱ የኤርትራ ወደቦች የነበረ በቢልዮን የሚገመተውን የመንግስትና የህዝብ ንብረት እንደዋዛ ለሻአብያ ተሰጥቶ መቅረቱን ለጊዜው
ትተን፤ ለዘመናት ያካበቱትን ሃብት ተዘርፈው በባዶ እጃቸውና ባዶ እግራቸውን፣ እየተደበደቡና እየተዋረዱ ከኤርትራ የተባራሩ
ኢትዮጵያውያን ቁጥር ያላቸውም። የአቶ መለስ መንግስት ይህንን ግምት ውስጥ ሳያስገባ ኤርትራውያን በኢትዮጵያ የነበራቸውን
ማንኛውም ንብረት መርፌ ሳይቀር መጥተው እንዲረከቡና ከፈለጉ እንዲሸጡ እንዲለውጡ እንዲሁም ተኩራርተው እንዲኖሩ
ለኤርትራውያን ጥሪ በማድረጋቸው፤ ሀገር የደፈረውን የኤርትራ መንግስት የእጁን ለመስጠት ራሳቸው መርቀው የላኩት ጀግናው
ፓይለታችን በዛብህ ጴጥሮስ ዓለም አቀፍ ሕግ ተከትለው የትደረስክ አላሉትም። የኢህአዴግ መንግስት ተቃዋሚ የሆኑት የፕሮፌሰር በየነ
ጴጥሮስ ወንድም መሆናቸው ውጪ ምን አርጎ ይሆን? ለአቶ መለስ ይህ አጋጣሚ ኢትዮጵያውያንን ሲክዱ የመጀመርያቸው አይደለም።
ለምሳሌ ለዘመናት ኤርትራ ሲኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በ1984 ዓ.ም ሃብት ንብረታቸውን በሻዕብያ ተወርሶ ከኤርትራ እንዲወጡ
ሲደረግ እነ ጠ/ሚ መለስ እንኳን ህዝባቸውን ወክለው የዲፕሎማሲ ስራ ሊሰሩ የችግሩ ሰለባ የሆኑና ያልሆኑ ዜጎችን ደም እያላወሱ
አቤቱታ ሲያቀርቡላቸው “የተወረሱትና ውጡ የተባሉት ‹የኢሰፓ› አባሎችና ቤተሰቦቻቸው እንጂ ንፁሃን ዜጎች ኣይደሉም” በማለት
አፌዙባቸው። በዛብህ ጴጥሮስ ንፁህ ኢትዮጵያዊ ስላልሆነ ይሆን እስከ አሁን በህይወት መኖሩና አለመኖሩ ሳይታወቅ ከዓለም አቀፍ ህግ
ውጭ ደራሽ ወገን ያጣ ዜጋ የሆነው? መቼም ሀገራዊ ኃላፊነት ተሸክሞ እንጂ ለግሉ ጥቅም ብሎ አይደለም አስመራ ሄዶ የተያዘው።
8ኛ. ከኢትዮጵያውያን ቦታ በመቀነስ ለኤርትራውያን የከፍተኛ ትምህርት Scholarship እንዲሰጥ በመፍቀዳቸው፤ ለምሳሌ በ2004
ዓ.ም በመቐለ ዩኒቨርሲቲ 52 ዲግሪ 18 ማስትሬት አንድ ሰው ዶክትሬት እንዲማሩ እንደተፈቀደላቸው የሚያሳይ መረጃ አለኝ።
(ትክክለኛውን ቁጥር ከመቐሌ ዩኒቨርስቲ ማግኘት ይቻላል። የትግራይ ክልል ሚድያዎችም ዘግበውት ነበር።)
በነዚህ ጉዳዮችና ሌሎች እኔ የማላውቃቸው ውለታዎች ኤርትራውያን ለጠ/ሚ መለስ ከህመማቸው እንዲድኑ ፀሎት ማድረጋቸው
ያንሳቸው እንደሆነ እንጂ አይበዛቸውም። እንዲያውም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ኣፈወርቂ ይህን ያክል እንክብካቤ ለኤርትራ ህዝብ
አድርገውለት አያወቁም።
“ከጠ/ሚ መለስ በኋላ ምን እንደሚመጣ እናውቃለን” እያሉ ስጋታቸው የገለፁ ያሉ ኤርትራውያን ግን ድህረ መለስ በተቃዋሚ ፓርቲዎች
በሚመሰረተው መንግስት ኢትዮጵያ በኢህኣዴግ አገዛዝ ያጣችውን ወደብ በህጋዊ መንገድ መጠየቋ እንደማይቀር ስለሚያውቁ ነው።
አዎ…አዎ የወደብ ጥያቄውንማ እኔም በግሌ የሚያግዘኝ ካገኘሁ ከመጠየቅ ወደኋላ አልልም። ኢህአዴግ ግን “ኢትዮጵያ መቼም ወደብ
ኖሯት አያውቅም” ብሎ ራሱ የኢትዮጵያ ባለ ጋራ ሆኖ መዝገቡን ይዘጋዋል። የወደብ ጥቅም ለኢህአዴግ ከሸቀጥ ያለፈ አይደለም።
ለኢትዮጵያውያ ግን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡
ደህና ሰንብቱ!
(ነሐሴ 15 ቀን 2004 ለንባብ ከበቃው ፍኖተ-ነፃነት ጋዜጣ የተወሰደ)
ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com
August 31, 2012

Advertisements
Categories: Uncategorized
  1. No comments yet.
  1. No trackbacks yet.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: