Home > Uncategorized > በ1984 ዓ.ም ሆን ተብሎ የተሠራው ጥፋት በ2004 ዓ.ም እንዳይደገም!

በ1984 ዓ.ም ሆን ተብሎ የተሠራው ጥፋት በ2004 ዓ.ም እንዳይደገም!

በ1984 ዓ.ም ሆን ተብሎ የተሠራው ጥፋት በ2004 ዓ.ም እንዳይደገም!

ተክሌ የሻው

የኢትዮጵያን ታሪክ፣ጥንታዊ ሥልጣኔ፣ውብና ድንቅየ ባህል፣ቅርስና የአገሪቱ ነፃነት ተጠብቆ መዝለቅ ሲነሳ፣በማንኛውም ንፁሕ ኅሊና ባለው ሰው አዕምሮ ውስጥ ቀድሞ ድቅን የሚለውAbune Merkorios Archbishop of Axum and Patriarch of All Ethiopian Orthodox church የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ነወ፡፡ ይህ ያለምክንያት አይደለም፡፡ የሃማኖቱ አባቶች፣ሕግ አውጥተው፣ሥርዓት ዘርግተው፣ሕዝቡ መንፈሳዊና ዓለማዊ ሕይዎቱን እንዲመራበት ያስቻሉ፤ክፉና ደጉን፣ጥሩውንና መጥፎውን፣ለይቶ እንዲያውቅ ያደረጉ ከመሆናቸውም በላይ፣ የግዕዝና የአማርኛ ቋንቋዎችን  ድምፆች ወካይ የሆኑ ፊደሎችን ቀርጸው ትውልድን  በተከታታይ ያስተማሩ ከመሆናቸው የተነሳ ነው፡፡ ሌጦን ፍቀው፣ አለስልሰውና አሳምረው ብራን በመሥራት መጻሕፍትን በመጻፍ ዕውቀትን ለትውልድ ያሸጋገሩ በመሆኑ ነው፡፡ ሥራ-ሥር ምሰው፣ ቅጠላቅጠል በጥሰው ወቅጠውና አቡክተው የተለያዩ ቀለሞችን በመሥራት ዘመን የማይሽራቸው ሥዕሎችን የሳሉ፣ሕንፃዎችን የገነቡ ስለሆነ ነው፡፡ በሌላ በኩል የሃይማኖቱ አባቶች፣ደሓ ሲበደል ፣ፍርድ ሲጓደል፣አይተው እንዳላዩ የማይሆኑ፣ “ድሓ ተበደለ፣ፍርድ ተጓደለ” በማለት ዓለማዊ መሪዎችን በመምከርና በመገሰጽ ድሓ እነዳይበደል፣ፍርድ እንዳይጓደል የማድረግ ኃይል የነበራቸው በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ አስገድዶ፣ሃይማኖትን የሚያስለውጥ፣ነፃነትን የሚገፍ ወራሪ ኃይል ሲነሳ፣ሕዝቡን በማስተባበርና በመቀስቀስ ወራሪውን ኃይል እንዲመክት በማድረግ የኢትዮጵያ ነፃነትና የሕዝቡ አንድነት ተጠብቆ እንዲዘልቅ ካደረጉት ጠንካራ ተቋሞች አንዱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በመሆኑ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተቋም፣ዕምነቱን በማስፋፋት ላይ ብቻ ያተኮረ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ የአገር ነፃነትና የሕዝብ አንድነት ዘብ፣የሕግና የሥርዓት ማዕድ፣የባሕልና የትውፊት ጎተራ በመሆኑ፣ለተስፋፊዎችና ቅኝ ገዥዎች ፍላጎት ምቹ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ይህም በመሆኑ ቅኝ ገዥዎች የአገሪቱን ጥሬ ሀብት ለመበዝበዝ፣ሕዝቡን ተዋራጅ ለማድረግ በተደጋጋሚ ያደረጉትን ሙከራ በማክሸፍ ወሳኝ ሚና ከተጫወቱት ተቋሞች መካከል አንዱ ስለሆነ፣ምዕራባውያን ተቋሙ በተቋምነት እንዳይቀጥል ያላደረጉት ጥረት እንደሌለ ይታወቃል፡፡ ጥረታቸውም ፍሬ አልባ አልሆነም፡፡ ከአያሌ ዘመን ተደጋጋሚ ጥረት በኋላ፣በኢትዮጵያ ታሪካዊና ወቅታዊ፣የሩቅን የቅርብ ጠላቶች ሁለንተናዊ ዕርዳታ የተደራጀው፣ የተመራውና ለሥልጣን የበቃው የወያኔ ጎሰኛና ዘረኛ ቡድን በ1983 የአገሪቱን የፖለቲ ሥልጣን እንዲጨብጥ ሲያደርጉ፣ የኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነነት መከታ የነበሩ ተቋሞች፣አስተሳሰቦችና አሠራሮች እስከ ወዲያኛው ሊያሰኝ በሚችል መልኩ እንዲያፈራርሳቸው አስደረጉ፡፡

የኢትዮጵያ ጠላቶች መሣሪያ የሆነው የወያኔ አገዛዝ፣በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመኑ የፈጸመው አገር የማፍረስ ተግባር አንዱ፣ የኢትዮጵያዊነት ሁለንተናዊ መገለጫ የሆነውን ፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አናት የሆነውን ቀኖና በማፍረስ ነው፡፡ “ፓትሪያሪክ እያለ ሌላ ፓትሪያሪክ አይሾምም” የሚለውን የሃይማኖቱን ዐምድ በመናድ፣ ሕገኛውን ፓቲሪያሪክ በማባረር፣በሃይማኖቱ ሕግና ሥርዓት ሳይሆን፣ፖቲካና ዘርን መሠረት ባደረገ መንገድ ፣ዛሬ ወደ ዕውነቱ ዓለም የሄዱትን፣(ነፍሳቸውን እግዚአብሔር ይማር፣የሠሩት ኃጢያት አምላክ ይቅር ይበላቸው) አባ ገብረ መድኅንን (አቡነ ጳውሎስ) ተካ፡፡ ይህ ተግባር ለዕውነት፣ ለሕግ የበላይነትና ለሃይማኖቱ ቀኖናና ዶግማ ተጠብቆ መዝለቅ ዕምነቱ ባላቸው የሃይማኖቱ አባቶች ተቀባይነትን ሊያገኝ አልቻለም፡፡ በመሆኑም ነባርና የሃይማኖቱ ጥልቅ ዕውቀትና ለሥራዓቱ መጠበቅ ቁርጠኛ አቋም ያላቸው አባቶች ፣ሕጋዊውን ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስን ጨምሮ በወያኔ የተሰጠውን የፖለቲካ ውሣኔ በመቃወም ወደ ስደት በማቅናት የተፈጸመው ስሕተት እንዲታረም ለኢትዮጵያና ለዓለም ኅብረተሰብ ድምፃቸውን በማሰማት ላይ መገኘታቸው ይታወቃል፡፡የአባቶች መሰደድ ጥንታዊቷን ቤተክርስቲያን ከሁለት ከመክፈሉም በላይ፣የሃይማኖቱን ተከታይ ሕዝብ እንደፖለቲካው ሁሉ በሁለት በመክፈል የሕዝቡን አንድነትና ሰላም በማናጋት ለጠብና ለውህከት እንደዳረገው በይፋ ይታያል፡፡

ላለፉት 21 ዓመታት ተቋሙና ተከታዩ ሕዝብ ወድ ጥፋትና መከፋፈል ጎዳና ያመራው የሃይማኖቱ ሕግና ሥርዓት፣ቀኖናና አስተዳደሩ በዘር ላይ በተመሠረተ አስተሳሰብ በፖለቲካ ውሣኔ በመሻሩ እንደሆነ ይታወቀል፡፡ የጥፋቱና የክፍፍሉ አንዱ አካል የሆኑት አቡነ ጳውሎስ በተፈጥሮ ሕግና በአምላክ ጥሪ ሳቢያ ይዘውት ከነበረው የሃይማኖቱ የመጨረሻ ሥልጣን ላይ መነሳት፣ሆን ተብሎ በ1983 በቤተክርስቲያኗ ላይ የተሠራው ስሕተት ፣ሊታረም የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ለቤተክርስቲያኒቱ ውስጣዊ ሰላም ማግኘት፣ለተቋሙ ኅልውና መረጋገጥና መቀጠል፣ለአማኙ አንድነትና ፍቅር ወደ ነበረበት ደረጃ ለመመለስ ይህን በእግዚአብሔር በራሱ የተፈጠረውን የሰላምና የአነድነት መልሶ መጎናጸፊያ ሁኔታ ግራ ቀኙ ወገኖች በአንክረሮ ተመልክተው በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ ይህን ለሰላምና ለአንድነት የተፈጠረን ምቹ ሁኔታ እንዳለፈው ሁሉ ዘረኛ ፖለቲከኞች ለኢትጵያ ጠላቶች ሊጠቅም በሚችልበት መልኩ ዳግም እንዳያደርጉት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና በተለይም የሃይማኖቱ ተከታይ ሕዝብ ነቅቶ መጠባበቅና በራሱ ፍላጎት ሥር እንዲውል በብረቱ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ዕውነተኛ የሃይማኖቱ አባቶችም ከምንጊዜውም በበለጠ ድምፃቸውን ለኢትዮጵያና ለዓለም ማኅበረሰብ ማሰማት የሚጠበቅባቸው መሆኑን ተረድተው ተከታዮቻቸውን በማስተባበር መጮህ ይጠበቅባቸዋል፡፡ይህም፡-

  1. ሕዝቡ እንዳለፈው በቸልታ ነገሩን ሳይመለከት፣ሕጋዊው ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ወደ ፕትርክና መንበራቸው  እንዲመለሱ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካሎች ድምፁን በማሰማት ሁለንተናዊ ጫና በአገዛዙ ላይ ማሳደር ይጠበቅበታል፡፡
  2. በየትኛውም ጎራ ያሉ የሃይማኖቱ አባቶች ዳግም ታሪካዊ ስሕተት እንዳይሠራ፣ለአገራችንና ለሕዝቡ አንድነት፣ለሃይማኖቱ ነባር ቀኖና ተጠብቆ መዝለቅ ፣ለተቋሙ ተጠናክሮ ሥራውን መቀጠል ሲሉ፣የየግል ፍላጎታቸውነ ወደ ጎን ትተው፣ለምእምናኑ አዘውትረው እንደሚያስተምሩት እነርሱም ለማያልፈው ሰማያዊ ሕይዎት ቅድሚያ ሰጥተው፣ምድራዊውን አላፊና ጊዜአዊ ነው ብለው

ለሃይማኖቱ ሕግና ቀኖና በዕውነት በመቆም ፣ለታሪክና ለትውልድ አኩሪ ተግባር ፈጽመው እንዲያልፉ የየበኩላቸውን መልካም ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋለወ፡፡

  1. ሕጋዊውና ስደተኛው ሲኖዶስ አስቸኳ ስብሰባ ጠርቶ ሁኔታውን በሰከነ መንገድ መርምሮ የተፈጠረው ሁኔታ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ትንሣኤ የሚሆንበትን መንገድ በመቀየስ ሕዝቡን በማስተባበር ታሪካዊ ኃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ ይጠበቃል፡፡
  2. ቀደም ሲል ለሰላምና ዕርቅ ቆመናል ያሉ ግለሰቦቸን ቡድኖች ዕውነትም ፍላጎታቸው የሃይማኖቱ ቀኖና እንዲጠበቅ ከሆነ፣ ለጥረታቸው ከፍተኛ መሰናክል ሆኖ የቆየው የሁለት ፓትሪያሪኮች ባንድ ጊዜ መኖር፣ የትኛውን አስወግደን የቱን እንተካው ፣ሥልጣኑ በማን እጅ ይቆይ፣ ሌላው የት ይቀመጥ የሚሉት አስቸጋሪ ጥያቄዎቸ እግዚአብሔር በፈቀደ የተመለሱ መሆናቸውን ተገንዝበው ዕውነተኛው ሰላምና አንድነት እንዲገኝ ቁርጠኝነቱና ፍላጎቱ ካላቸው ይህን አጋጣሚ በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ በፖለቲካ ውሣኔና በዘር ላይ የተመሠረተው የቀኖና ሽረት ተሸሮ፣ቀኖናው ወደነበረበት መመለስ ካልተቻለ፣ለሃይማኖቱም ሆነ፣ለተቋሙ ዳብሮ መቀጠል ትቶት የሚያልፈው ቁስል አመርቃዥ እንጂ፣ሻሪ/ዳኝ) አለመሆኑ ታውቆ፣ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በቅን ልቦና ፣በንፁሕ ኅሊና፣ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መቀጠል ሲሉ ጥቃቅንና ዕለታዊ ጥቅሞቻቸውንና ፍላጎቶቻቸውን ወደ ጎን ብለው ኃይላቸውንና ዕውቀታቸውን አስተባብረው መሆን የሚገባው ጉዳይ መሆን ባለበት ወቅትና ጊዜ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ እንዲሆን በማድረግ ትውልዳዊ አደራና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ይጠበቃል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ፡፡

አሜን!

Advertisements
Categories: Uncategorized
  1. No comments yet.
  1. No trackbacks yet.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: