Home > Uncategorized > ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት በሥልጣን ላይ ላሉትና ከዚያ ውጭ ላለነው በጣም ትልቅ ነገር ያስተምራል ብዬ አምናለሁ››

‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት በሥልጣን ላይ ላሉትና ከዚያ ውጭ ላለነው በጣም ትልቅ ነገር ያስተምራል ብዬ አምናለሁ››

‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት በሥልጣን ላይ ላሉትና ከዚያ ውጭ ላለነው በጣም ትልቅ ነገር ያስተምራል ብዬ አምናለሁ››

SUNDAY, 26 AUGUST 2012 00:00
BY A STAFF REPORTER

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ

ዜናው በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ በዋናነት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ሰው የሰው ፍጡር በመሆኑ ከዚያ በኋላ ደግሞ የአገሬ ሰው በመሆኑ በጣም አዝኛለሁ፡፡ ሰዎች ከአቅማቸው በላይ በሆነ በተፈጥሮ ችግር በበሽታ ሲሰቃዩ ወይም ደግሞ በሞት ሲያልፉ መደሰት እኔ ተፈጥሯዊ አይመስለኝም፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተሰቦች ሐዘን ቢሰማኝም ከዚያ በላይ ግን ለአገራችንም ለሁላችንም በጣም አዝኛለሁ፡፡ ይህን የምልበት ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣን በቆዩባቸው 21 ዓመታት ውስጥ ብዙ ዕድሎች አምልጠዋል፡፡ አገራችን ወደተሻለ የፖለቲካ ሥርዓትና ሁሉን አቀፍ ወደ ሆነና ዜጎች ሥልጣን ያላቸው እንዲሆኑ ለማድረግ ብዙ አጋጣሚዎችና ዕድሎች አልፈዋል፡፡ እንደኔ ሐሳብ ከሆነ እኚህ መሪ በእነዚያ ዕድሎች ተጠቅመው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ይኼ ሐዘን በሌሎች አገሮች ላይ እንደሚሆነው ሁሉ በሞት የተለየው ሰው ስላደረገው ጥፋት፣ ስላደረገው ኃጢያት ወይም ስለወንጀሉ ሳይሆን እንደ መሪያችን አጣነው በሚል እንደ ሕዝብ አንድ ላይ ሐዘን ብንቀመጥ እንችል ነበር፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ግን እንደዚያ ስለማያሳይ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ 

እርሳቸው ለሁለት ወር ኃላፊነታቸው ላይ ሳይገኙ በሕመም ሲሰቃዩ ነበር፡፡ ይህም መረጃ ለሕዝብ ሳይገለጽ በጣም በከፍተኛ ሥርዓትና ጥንቃቄ መንግሥት ሁኔታውን ይዞ ቆይቷል፡፡ ያ የሚያሳየው የፖለቲካ ሒደቱ ዜጎች ባለቤትነት ተሰምቷቸው፣ የራሳቸው ጉዳይ አድርገውና ፖለቲካው ላይ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ስላልኖሩና አጠቃላይ ሥርዓቱ በግለሰብ ማንነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ሥልጣን ላይ ያለው ሁሌ ሕዝብን እየፈራ መኖሩን ነው፡፡ ይህ በመሆኑ በጣም ያሳዝናል፡፡ መንግሥታችንም የራሳችን መንግሥት ነው፡፡ የአገራችን ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነው፡፡ መሪዎቹ ላይ የሚደርሰው ጥፋት ወይም ጉዳት የሁለችንም ጉዳት ነው፡፡ ስለሕዝብ ብለን የምንኖርበት አገር ሐዘናችን የጋራችን የሚሆንበት አገር ሆኖ ማየት ሁሌም የምፈልገው ነው፡፡ ቢሆንም ግን ያንን ችግራችንን በትልቁ ያሳየ ሁኔታ በመግጠሙ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ ለአገርም፣ ለራሴም፣ በሞትም ለተለዩት ሰው፣ ለቤተሰቦቻቸውና በአጠቃላይ ይኼ የሐዘን ሰዓትና ጊዜ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡

በዚህ ሥርዓት ከተጎዱት ሰዎች መካከል አንዷ እኔ ነኝ፡፡ ከእኔም በባሰ ሁኔታ የተጎዱ ሰዎች አሉ፡፡ በዚህ ሰዓትም በእስር ቤት የሚሰቃዩ ሰዎች አሉ፡፡ ሕይወታቸውንም በግፍ ያጡ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ያ እንዲሆን ያደረገ ሰው በሕመም ሲሰቃይ ወይም በሞት ሲያልፍ ማየት የእኛን ጉዳት በፍፁም አይጠግነውም፡፡ ጉዳታችንን በፍፁም የምንረሳ ወደኋላ የምንተወው አይደለም፡፡ የምንካሰው ያሰቃየንን ሥርዓት፣ ያሰቃየንን አሠራርና አስተዳደር ተለውጦ ስናይ ነው፡፡ አልሆነም እንጂ ቢሆን ኖሮ አቶ መለስ ሐሳባቸውን፣ አካሄዳቸውንና ፓርቲያቸውን ቀይረው፣ የብሔራዊ እርቅ አካል ሆነውና ነፃነትና ዲሞክራሲ እንዲሁም የኢኮኖሚ ብልፅግና የሰፈነበት አገር አብረን መሥርተን የዚያ አካል ሆነው በሞት ቢለዩ ወይም ከሥልጣን ቢለቁ ትልቅ ቅርስ ትተው ቢያልፉ ኖሮ ደስታዬ በጣም ትልቅ ይሆን ነበር፡፡ ይህን የምለው ሳልጎዳ ቀርቼ አይደለም፡፡ ነገር ግን በስህተት ውስጥ ያለፉ ሰዎች ስህተቱን የማረም፣ ጥፋትን መቀበል፣ የሰዎች ሕይወት በግፍ ማለፉ፣ ሕግ አለአግባብ ሥራ ላይ መዋሉና የግፍ መሣርያ መሆኑ ትክክል አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላ አገራችንን በሌላ አቅጣጫ መምራት አለብን በሚል ሒደት ውስጥ አለማለፋቸው በጣም ያሳዝናል፡፡ 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት በሥልጣን ላይ ላሉትም፣ ከዚያ ውጭ ላለነውና ለዜጎችም በጣም ትልቅ ነገር ያስተምራል ብዬ አምናለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ21 ዓመታት ሥልጣን ላይ ቆይተዋል፡፡ ከዚያ በፊትም ፓርቲያቸውን ይመሩ ነበር፡፡ በትጥቅ ትግሉም ተሳትፈዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት አሁን ላይ ሆኜ በዚህ ጊዜ እንዲህ አደረጉ በዚህ ጊዜ እንዲህ አሉ ማለት አልችልም፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ ያሳዩት የነበረው ሁኔታ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር እንደሚችሉና እንደፈቀዳቸው የአገርን ዕድል መወሰን እንደሚችሉ አድርገው ነበር ሥራቸውን ሲያከናውኑ የነበረው፡፡ እንደ ሰው እዚህ ምድር ላይ ያለን ዕድል ውስን እንደሆነ የመዘንጋት ነገር በእርሳቸውም ሆነ በተከታዮቻቸው ዘንድ ተስተውሏል፡፡

ለዚህም ይመስለኛል ሥልጣን በሙሉ አንድ ሰው ላይ ሲጠራቀም፣ እርሳቸው ሁሉንም ነገር ማከናወንና የዕይታ ማዕከል ሲሆኑ፣ ሁኔታውን እንደ ትክክለኛ ነገር በማየት ነበር ሥራቸውን ሲሠሩና አገራቸውን ሲመሩ የቆዩት፡፡ ይሁንና በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ የተፈጠረው ነገር ታይቷል፡፡ በጣም ለረጅም ጊዜ እቆያለሁ የሚል ሰው በዚህ ሁኔታ መንገዱ ተቋረጠ ማለት ነው፡፡ ለነገሩ እኛ ሰዎች ስንባል ሟች በመሆናችንን፣ ሁሉን ቻይ ባለመሆናችን፣ ፍፁም ባለመሆናችንና ሁሉንም ባለማወቃችን ምክንያት ነው ዲሞክራሲ የሚያስፈልገን፡፡ በአንድ ሰው ሥልጣንና በአንድ ሰው ሥራ የአገር ሁሉ ዕድልና ፈንታ መወሰን የለበትም የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሁኔታ ሁላችንም መማር እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡በተለይ ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ይህንን ማሰብና ማስተዋል ይገባቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

ማንም ነፃ አገር ላይ እንደሚደረገው ሥልጣን መከፋፈል አለበት፡፡ የሥልጣን ማዕከሎች የተለያዩ መሆን አለባቸው፡፡ ኅብረተሰቡ የራሱ ሥልጣን ሊኖረው ይገባል፡፡ ዜጎች ሊበረታቱ ይገባቸዋል፡፡ ዜጎች ባለመብት መሆን አለባቸው፡፡ የአገሪቷ ተቋማት በየሁኔታቸው መሥራት መቻል አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ነች ብዬ ነው የማምነው፡፡ ሰማንያ ሚሊዮን የሆኑ ዜጎች ዕድላቸው በዚህ መንገድ ሊመራ አይገባም አይችልምም፡፡ ስለዚህ ከዚህ ትምህርት ወስደው ለአገራቸው፣ ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸው ደህንነትና እንሠራለታለን ለሚሉት ቡድንም ዘለቄታዊ መተማመኚያ የሚሰጠው ነፃ የሆነ፣ የሕግ የበላይነትን የሚያከብርና ሥልጣንን በሚያከፋፍል ሥርዓት ለመሥራት መነሳት አለባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ታሪካችን መለየት መቻል አለብን፡፡

ትልቁ ትምህርትና ለውጥ የሚጠበቀው ሥልጣን ላይ ካሉት ኃይሎች ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ከሆነ የቀረው በጣም ቀላል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች በጣም ሥልጡን ናቸው፡፡ ያልተማሩና ገንዘብ የሌላቸው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ሕግን የሚያከብሩ፣ በሰላም የሚገዙና ግጭትን የማይወዱ ዜጎች ናቸው፡፡ ተቀዋሚዎችም ይህንን ወደፊት ለማስኬድ ዝግጁነት አላቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ቢሆንም ግን ትልቁ ለውጥ ሥልጣን ላይ ካለው ኃይል ይጠበቃል፡፡ ሁሉን አቀፍ ሥርዓት መገንባት አለብን ማለት አለባቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ፕሬዚዳንት የነበሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አሜሪካ በትምህርት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ አስተያየት የተወሰደው ከአውራምባ ታይምስ ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ ነው፡፡ 

Advertisements
Categories: Uncategorized
  1. No comments yet.
  1. No trackbacks yet.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: