Home > Uncategorized > የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የለንደን ቆይታው ወጪ ኦዲት እንዲደረግ ተጠየቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የለንደን ቆይታው ወጪ ኦዲት እንዲደረግ ተጠየቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የለንደን ቆይታው ወጪ ኦዲት እንዲደረግ ተጠየቀ

August 15, 2012
  • በልዑካኑ ቡድን ላይ የገቢዎችና ጉምሩክ ጥብቅ ፍተሻ እንዲያደርግ ተጠየቀ 
  • የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሎተሪ ዕጣ ኦሎምፒኩ ከተጠናቀቀ በኋላ መቀጠሉምአነጋጋሪ ሆኗል

በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ውስጥ የአለም አቀፉ አማተር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባዘጋጀው 30ኛው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ልዑካን በለንደን ቆይታው ያወጣው የወጪ አፈፃፀም ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን አንዳንድ የሕብረተሰቡ ክፍሎች ጠየቁ።

በዚሁ በለንደን ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ቁጥር ከውድድሩ ተካፋይ አትሌቶች ቁጥር በላይ በመሆኑ፤ የመንግስትና የሕዝብ ገንዘብ በተገቢ ቦታ ላይ መዋል አለመዋሉን ማረጋገጫ መቅረብ አለበት ሲሉ ጠይቀዋል።

በለንደን የነበሩ የአይን እማኞች ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለጹት፤ “በቁጥር ወደ ስልሳ አምስት የሚጠጋው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ልዑካን ቡድን ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት የኮሚቴ አባላት ናቸው። አብዛኛዎቹ ኮሚቴዎች በለንደን ሱቆች ውስጥ የተለያዩ ዕቃዎች ሸመታ ላይ የሰነበቱ ሲሆን፤ በጣም በጣት የሚቆጠሩት ውድድሩን ሙሉ ለሙሉ ተከታትለዋል። ይህን ለማረጋገጥ የፈለገ የመንግስት አካል የልዑካን ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ጠበቅ ያለ የጉምሩክ ፍተሻ ማድረግ በቂ ነው። በተለይ በልዑካን ስም የሸመቱትን እቃዎች ቀረጥ ሳይከፍሉባቸው ለማስገባት ስለሚሞክሩ መንግስት ከፍተኛ የጉምሩክ ፍተሻ በልዑካኑ ቡድን ላይ ማድረግ አለበት። ይህን ድርጊት መግታት ካልተቻለ በሕጋዊ መንገድ እየሰሩ ያሉትን ነጋዴዎች ገበያ የሚያፋልስ ድርጊት ከመሆኑ በላይ፤ ወደፊት በዚህ መልኩ ሊሰለፉ የሚፈልጉ የፌዴሬሽን አመራሮች መፈጠራቸው አይቀርም” ብሏል።

እንደ ዓይን እማኙ ገለፃ፤ “በአስር ሺ ሜትር ውድድር ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም የጡንቻ መሰንጠቅ ጉዳት ሲያጋጥመው ተጠባባቂ አትሌት የሆነውን ሌሊሳ ደሲሳ ይዘው ባለመሄዳቸው ለውጤት ማጣት መንስኤ ሆኗል። በቴሌቪዥን ለሚከታተል ሰው የገ/እግዚአብሔር ጉዳት ብዙም ላይታየው ቢችልም በስታዲየም ውስጥ ለታደምነው ሰዎች ግን በጣም አሳዛኝ አጋጣሚ ነበር። ቢያንስ ይህ ሁሉ ኮሚቴው ከሚጓዝ አንድ የአስር ሺ ተጠባበቂ አትሌት ይዘው መሄድ ነበረባቸው። ይህን መሰል በሀገር ላይ የተደረገ ሸፍጥ መንግስት ዝም ብሎ ሊያልፈው የሚችል ጉዳይ አይመስለኝም። በጣም የሚገርመው ደግሞ፤ በቅርብ ጉዳዩን ለመከታተል ፈልገን ወደ አትሌቶች እንዳንቀርብ ከልክለውናል” ሲል አስረድቷል።

ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቅርብ የሆኑና ስማቸው እንዳይገልጽ የፈለጉ ባለሙያ እንዳሉት፤ የልዑካን ቡድኑ “በለንደን ቆይታቸው ወጪ ያደረጉትን ደረሰኞች አግባብነት መንግስት በኦዲት ሊያስመረምረው ይገባል። የወጪዎቹ ሕጋዊነት ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው ለተገቢ ስራ ሄዶ ወጪ የተደረገለት መሆኑን ምርመራ መደረግ አለበት። የሕዝብ ገንዘብ በአደባባይ በጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ወጪ ሊደረግበት አይገባም። ይህን ድርጊታቸውን መከላከል ካልቻልን ወደፊት ሕዝቡ አትሌቲክሱን ለመደገፍ በሚያደርገው ተሳትፎ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። ስለዚህም የህዝብ ገንዘብ በአግባቡ መዋሉን በይፋዊ ሪፖርት ሊረጋገጥ ይገባል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ አያይዘውም ተንጋግተው ለንደን የተጓዙት የኮሚቴ አባላት አለአግባብ የሕዝብ ሐብትን ያባከኑ በመሆናቸው የፌዴራሉ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም ሲገቡ ጥብቅ ፍተሻ በማድረግ ረገድ የገቢዎች ጉምሩክ ባለሥልጣን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

 ሌላው፤ የኦሎምፒክ ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ያዘጋጀው የሎተሪ ጨዋታ ማካሄድ ለምን አስፈለገ ተብሎ ጥያቄ የቀረበላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሎተሪ የማስታወቂያና ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ንዋይ በሰጡት ምላሽ፤ “ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር የፈፀምነው የሎተሪ ዕጣ ስምምነት ከመጋቢት 1 እስከ ነሐሴ 13 የሚቆይ ነው። ውድድሩ አልቆም የሎተሪው ዕጣ ቀጣይነት እንዳለው በፊት ሁለታችንም የገባነው ስምምነት በመሆኑ የሕግ ችግር የለበትም። እየተደረገ ያለው የሎተሪ ዕጣ ሕጋዊ ነው” ብለዋል።

“የኦሎምፒክ ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ገንዘብ መሰብሰብ እናንተ ቀደምብላቹሁ መስማማታችሁ ብቻውን ሕጋዊ ያደርገዋል ወይ?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ስምምነት ስንፈጽም ምን ያህል ገንዘብ ሊሰበሰብ እንደሚችል ማንም አያውቅም። ከጠበቁት በላይ ወይም ከሚያስፈልጋቸው በላይ ገንዘብ ሰብስበዋል የምትል ከሆነ፤ እነሱን ነው መጠየቅ የምትችለው። እኛ ያደረግነው ግን መመሪያው በሚፈቅደው መሠረት መሠራቱን ላረጋግጥ እችላለሁ” ሲሉ አቶ ቴዎድሮስ መልስ ሰጥተዋል።

ሰንደቅ ጋዜጣ 7ኛ ዓመት ቁጥር 362 ረቡዕ ነሐሴ 9/2004Image

Advertisements
Categories: Uncategorized
  1. No comments yet.
  1. No trackbacks yet.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: